25 አመት በሙሉ ለማንም ሰው ተናግሬ አላውቅም። ግን ያኔ የሉላደይን መፅሃፍ የሰረቀው ተብዬ በአደባባይ ተገርፌያለሁ። "ሌባ ሌባ ሌባ" እያሉ እየተከተሉ ዘፍነውበኛል። ከመገረፉ በላይ ዘፈኑ ያም ነበር። የሉላደይን እንግሊዘኛ መፅሃፍ በእጄ ይዤው ወደ ቤት ስሄድ እጅ ከፍንጅ ተይዤ ነው፤ ሰርቄ ግን አይደለም______ ማርያምን። መጀመሪያ "አንተ ሌባ" ከሚል ንግግር ጋር ቆንጅዬ ኩርኩም ቀመስኩ። በዛ ቅፅፈት ምን አድርጌ እንደነበር ሊገባኝ አልቻለም። መፅሃፉን ከእጄ ሲነጥቁኝ ግን ሌብነቱ ከመፅሃፉ ጋር እንደሚገናኝ ተገለጠልኝ። በወቅቱ መፅሃፉን በእጄ ብይዘውም ማን በእጄ እንዳስያዘኝ ግን አላወኩም ነበር።
ከኋላዬ "ሌባ ሌባ ሌባ" እያሉ እያጀቡኝ ነው። ንፁህ ሰው ስለነበርኩ ዱላው አላስለቀሰኝም። "ሌባ ሌባ..." የሚለው ድምፅ ግን ይሰቀጥጥ ነበር። ዞሬ አየኋቸው። ያየሁትን ቶሎ ነው ፎቶ የማነሳው። ወደ ቀኝ ወደ ግራ አየሁ። ያጨበጨቡ፣ ጮክ ያሉ፣ ፈገግ ያሉ፣ የደንሱ ሁሉንም አንድ በአንድ በፎቶ ማህደሬ ውስጥ አስቀመጥኩ። እጅግ ያሳዘነኝ ነገር ግን አንድ ሰው እንኳ ላይሰርቅ ይችላል ብሎ አለመገቱ ነው። ሉላደይ እንኳ ያንን የሚያሳዝን ፊቷን ያሳየቺኝ "ሰርቋል! ግን ለምን ሰረቀ?" ብላ ነው። እጅግ ሲበዛ አዘንኩ።
አንድ ሳምንት እስኪረሳሳ ጠበኩና ጥናት አረኩ። የነገሩን ጠንሳሽ፣ አቀናባሪ፣ አሰፈፃሚ ሁሉንም አንድ በአንድ ደረስኩባቸው።
**** **** *****
ከአራተኛ ክፍል በኋላ እንዲህ ሆኖ አያውቅም ነበር። 8ኛ ክፍል እያለን የሆነ ክፍለ ጊዜ ላይ ክፍላችን በአንድ እግሩ ቆመ። አራተኛ ክፍል ሙዚቃ ፔሬድ ላይ ያለን ነበር የሚመስለው። ዋሲሁን ነበር አስጀማሪው......
"አሌ ጀናው__ ጀናው
አሌ ጀናው__ ጀናው
ኮፍያው ቀዳዳ
ጫማው ሚስማር የለው
ቢመታ ቢመታ
ታምቡር እየመታ
አልዬ አሌ__ አሌ
አሌ ሰላሌ
የኮልፌ ተማሪ ምኑን ተማረችው
አጥር ተድግፋ ና ሳምኝ አለችው
አሌ ጀናው__ ጀናው...
ክፍሉ በአንድ እግሩ ቆመ።
የትምህርት ቤታችን ሁነኛ ገራፊ ቲቸር ባነተአምላክ ያንን እባብ ጎማቸውን እያወዛወዙ እስኪገቡ ድረስ ጫጫታው እንደቀጠለ ነበር። ሁላችንም ደብተር ቦርሳችንን ይዘን ተከታትለን እንድንወጣ ተነገረን። የሁካታው አስጀማሪ ዋሴ የድግስ ጠላ ጠጥቶ ነበር የመጣው። ቢገረፍም አይገባውም። እኛ ግን አንድ በአንድ እየተገረፍን ከነ ህመማችን፣ በሁለት ወንዶች መሃል አንዳንድ ሴት እየተመደበልን እንድንቀመጥ ተደረገ። በወንዶች መሃል ሴት ማስቀመጥ አራት አምስተኛ ክፍል የቀረ ፋሽን ነበር። አላማው እንዳንረብሽ መሆኑ ነው__ ሴት እንድናፍር።
በዚ መሃል ነው እኔና ከሪም ሉላደይ የደረሰችን። አራተኛ ክፍል እያለን ሴት መሃላችን ሲያስቀምጡ ዝም ዝም ነበር መልሳችን። ስምንተኛ ክፍል ደርሰን ግን ይሄ ሲሆን "ማን ደረሳችሁ? ማን ደረሳችሁ?" ሆነ ወሬያችን። አሁን ድረስ ኤፍሬም ታምሩ "ታድሏል አካሌ ይዟል ድርሻውን" ብሎ ሲዘፍን ሉላደይ ትዝ ትለኝና ፈገግ እላለሁ።
የመጀመሪያው ቀን የተገረፍነው ዱላ ስለሰራ ይመስለኛል ፀጥ ረጭ ብለን ነበር ያሳለፍነው። እኔን ግን ሁለተኛው ቀን ጠዋት ላይ ትምህርት ቤት ለመድረስ የቀደመኝ የለም። ሁለተኛው ረድፍ ሶስተኛው ዴስክ ላይ በግራ በኩል ነው የምቀመጠው። ሉላደይ መጣች። ገና ከበር ስትገባ ነበር ያየኋት። የሞቢል ሰራተኛ የሚያስመስለን ዩኒፎርማችን እንደሷ የሚያምርበት ሰው ያለ አይመስለኝም። ዲኖ ቦርሳዋ ክንፍ፣ አዲዳስ ጫማዋ ደግሞ ደመና ነው የመሰለኝ። እየበረረች ወደኔ ስትመጣ አስታውሳለሁ።
አጠገቤ ደርሳ "አሳልፈኝ እንጂ" ብላ ያን የጠዋት ጥርሷን እስክታሳየኝ ድረስ በራሪ ነገር እንጂ ተራማጅ ፈጥረት አልጠበኩም። ላሳልፋት እንዴት ወደ ውጪ አቅጣጫ እንደዞርኩ አላወኩም። "ደና አደርክ" አልቺኝ። ፈገግታዋ አልጠፋም። ጥረሷ ላይ ነበርኩና "አለን በአዲዳስ" አልኳት። "መች ታዲያስ አለኩህ?" ስትለኝ ነው ወደ ቀልቤ የተመለስኩት። 'ታዲያስ' ያለቺኝ መስሎኝ ነበር። በወቅቱ ታላላቆቻችን 'ታዲያስ' ሲባሉ 'አለን ባዲዳስ\ የሚል ፋሽን አምጥተው ነበር። በኔ ቤት ያንን መከተሌ ነበር።
"ደና አደርክ እኮ ነው ያልኩህ!" ቀጠለች። ፈገግታዋ ሊገለኝ ነው። "ደና" ብዬ እጄን ዘረጋሁላት.... ግራ እየገባት እጇን ሰጠቺኝ። በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ የሚያምር ጣት እንደነካሁና እንደነዘረኝ ታወቀኝ። እጇን ይዤው ቆየሁ። ይዤው ብሮጥና ለማንም ባላሳየሁ ሁሉ ተመኝቼ ነበር። ቀስ ብላ እጇን ወሰደችብኝ።
**** **** *****
ስለ ሉላደይ ሌላ ጊዜ በሰፊው ስለምነግራቹ ወደ መፅሃፉ እንመለስ። ብቻ የኔና ሉላደይ ትውውቅ የጀመረው እንደዚህ ነበር። ብዙ ነገር ታወራኛለች። እሰማታለሁ። ጥቂት ነገር እነግራታለሁ። ታዳምጠኛልች። በጣም ተግባባን። የብዙ ተማሪዎች አይን ውስጥም ገባን። የተለየ የነበረው ግን የቁምላቸው ግርማ ነበር። ቁምላቸው ከኛ በእድሜ ትንሽ ከፍ የሚል ልጅ ነው። በረፍት ሰአት ላይ ጮርናቄ ይገዛልኛል። ምሳ ሰዓት ላይ እንደ ልጅ በረዶ ይገዛልኛል። ሉላደይን እንደፈለጋት ገብቶኛል።
አንድ ቀን የከሰዓቱን ትምህርት ጨርሰን ወደ ቤት ስንሄድ ___ 9፡30 ላይ ቁምላቸው ተከተለኝ። ቀጥታ ነው "የነ ሉላደይን ቤት አሳየኝ" ያለኝ። "ደክሞኛል ቤታቸው ሩቅ ነው" አልኩት። መጀመሪያ ከፈለክ ቤቷን ተከትለህ አታይም ወይ ልለው ነበር። በኋላ ሳስበው ያላሰበውን ማሳሳብ ሲሆንብኝ ጊዜ ተውኩት። ቢመታኝ ደስ ይለው ነበር። ግን እንዴት ይምታኝ ተይዟል። ዝም ብሎኝ ተመለሰ።
ክፍል ውስጥ እያለን ይመጣና እስኪ ጠጋ በል ብሎኝ የባጥ የቆጡን አውርቶኝ ይመለሳል። ለሱ ስጠጋለት ለሉላደይ የበለጠ መቅረቤን ግን የተገለጠልት አልመሰለኝም። ምንም የማይፈራ ልጅ እሷን በጣም ይፈራታል። ስላላወቀ እንጂ የኔ ሉላዲ የምታስፈራ ልጅ አልነበረችም።
ከብዙ ጮርናቄና ከብዙ በረዶ በኋላ ከኔ ጠብ የሚል ነገር ሲያጣ ሰለችው። ስለ ሉላደይ ብዙ ማወቅ ይፍልጋል። የሚያውቀውን እንጂ ምንም አዲስ ነገር አልነግረውም። በዚ መሃል ሉላደይ እያደገች እየጎመራች መጣች። አጎጠጎጤ አወጣጧን ለውጡን እንኳ አስታውሰዋለሁ። በዛው ልክ ፂም የሚጀማምራችው ልጆችም ተፈጠሩ። የሉላዲ ፈላጊዎች እየበዙ መጡ። እኔ ግን እሾህ አጥሯ ነበርኩ። በኔ በኩል አልፎ አንድም ሰው አያገኛትም። ተደራጁብኝ።
ይሄኔ ነው ቁምላቸው ብርጌድ በይፋ የተቋቋመው። በዋነኝነት ቁምላቸው ግርማን፣ ሰብስቤ በጋሻውን፣ እዮብ ፋንታሁንን፣ ጀሚል አህምድን፣ በፀሎት አረፋይኔን ይዟል። የዚ ብርጌድ እያንዳንዱ አባል በማወቅም ባለማወቅም ከሉላድይ እንግሊዘኛ መፅሃፍ ስርቆት ጀርባ እጁ አለብት።
ሰብስቤ በጋሻው
የነ ሉላደይ ጎረቤት ነው። አንድ አጥር ነው ነው የሚለያቸው። ከሌላ ሰው በተለየ ስለ ሉላደይ በቅርብ እንደሚያውቅ ይሰማዋል። እኔን "ሌባ ሌባ ሌባ" እያሉ እየተከተሉ የሚዘፍኑልኝ ቀን 87 ህገመንግስት የፀደቀ ጊዜ ፓርላማ ላይ እያጨብጨቡ እንደሚጨፍሩት ሰውዬ ነው አኳሃኑ። እየዘለለ ነው "ሌባ ሌባ" የሚለው። ሁኔታው ያበሽቅ ነበር። ሉላደይ ከሱ በላይ እኔን ስለምትቀርበኝ ይናደድ ነበር። "አጥራችን ባይኖር ቤታችን ቤታቸው ነው በጣም የምታውቃት እንዳይመስልህ" ቃል በቃል ያለኝ ነው። በቁምላቸው ሃሳብ አመንጪነት የሉላደይን እንግሊዘኛ መፅሃፍ ከቤቷ የሰረቀው እንግዲህ የቅርብ ጎረቢቷ ሰብስቤ ነው።
ቅጣት 1
ሰብስቤ በጋሻው መቀጣት አለበት ብዬ አምኛለሁ። አምኜም ወደ ተግባር ገብቻለሁ። ሰብስቤ እሁድ ቀን እድር ሊከፍል እኛ ሰፈር ይመጣል። ውሻ ይብላውና ውሻ በጣም ይወዳል ደሞ። አንድ እሁድ በጠዋት ትንሽዬ ቡችላ ይዤ በመንገድ ጠበኩት። ገና ሲያየኝ ምራቁን ማዝረብረብ ነው የቀረው። እንዲያሻሻት ሰጠሁትና ምግብ እንዳልበላች ነገርኩት። "ከፈለክ ትንሽ ትደግና ትወስድታለህ" ጉጉት ጨመርኩለት። በደስታ ጮቤ ረገጠ። ሰከረ ነው የሚባለው። ሰው ሲሰክር ደግሞ የሚያደርገውን አያውቅም። ከእድሩ ክፍያ ላይ አምባሻ ገዝቶ ለቡቺ ሲሰጥ የሞቀ ስካር ውስጥ ነበር። ቡችላ መቀየር ከፈለገ አማራጭ እንዲያይ ወደ እናትዬው ወሰድኩት። እውነት ለመናገር ለሁሉም ቡችሎች ለእናትዬውም ጭምር አምባሻ እንዲገዛ ማድረግ የኔ ምኞት አልነበረም። የኔ ሃሳብ እድሩን ሳይከፍል ቤት መመለሱና የጋሽ በጋሻውን ታዋቂ ጡጫ እንዲቀምስ ብቻ ነበር። ግን እሱ ደግ ነው። እድሩን ካለመክፈል አልፎ ሳንቲሙን ጭጭ አርጎ ቤቱ ገባ።
በማግስቱ ትምህርት ቤት ሲመጣ ከሪንግ አምልጦ የመጣ ቦክሰኛ ይመስል ነበር። ትንሽ አሳዘነኝ። እኔ በሱ የተነሳ የተገረፍኩት ምልክት አልተወም ነበር። የሱ ግን የእድሜ ልክ ጠባሳ ሆኖ እንድሚቀር ያንኑ ቀን ያስታውቅ ነበር። ይሄ ስለፀፀተኝ የውሸት ልሰጠው ቃል የገባሁለትን ቡችላ የእውነት ሰጠሁት።
ሰብሰቤ አሁን አደገኛ ባንከር ሆኗል። ታማኝ ከፋይ ነው ይሉታል። ከሰው ብር አንስቶ ለቡችላ ምግብ አለመግዛት ያኔ በእንቁላሉ ጊዜ እንዲማር አድርጌዋለሁ። ሰብስቤ ሆይ ከ25 ዓመት በኋላ የራስህን ጠባሳ እውነተኛ ታሪካዊ አመጣጥ የምነግርህ፣ ምን ያህል ጠቃሚ ትምህርት እንዳስጨበትኩህ አስታውሼ እንድታመሰግነኝ ነው። አሁን "ጎበዝ ከፋይ ነው" ቢሉህ ... "ታማኝ ከፋይ ነው" ቢሉህ ... "እድሜ ለሱ" እያልክ ጠባሳህን በመስታወት ጎብኘት አርገው ሃሃሃ
እዮብ ፋንታሁን
እዮብ ፋንታሁን የቅርብ ወዳጄ ነው። የልቤ ሰው። ሚስጥሬን፣ ደካማና ጠንካራ ጎኔን በሙሉ ያውቃል። በጦፈ ወሬ መሃል ሆኜ ዕቃ ሲሰጡኝ ዕቃውን ሳላይ እንደምቀበል ጠንቅቆ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው። ይሄንን ድክመቴን ለቁምላቸው ብርጌድ አሳልፎ የሰጠው እሱ ነው። ሰብስቤ ከነ ሉላደይ ቤት ሰርቆ ያመጣውን መፅሃፍ በወሬ መሃል በእጄ ያስጨበጠኝም የልቤ ሰው እዮቤ ነው። ለዚህ ውለታው ከቁምላቸው 2 ብር ተቅብሏል። እዮቤ እኔን ጓደኛውን በሁለት ብር ሸጠኝ። የሰፈር የሹራብ ማልያ መግዣ ሳንቲም ይፈልግ እንደነበር አውቃለሁ። ሳይጠይቀኝ "እስከ ቅዳሜ ታገሰኝ እኔ እሰጥሃለሁ" ብዬው ነበር። መታገስ አቃተና እኔን ጓደኛውን ልሰጠው ቃል በገባሁለት 2 ብር ሸጠኝ።
ቅጣት 2
ባዮሎጂ አስተማሪያችን ቲቸር ፍቅሩሰው እንደሚጠጡ ይታወቃል። በገንዘባቸው ነው የሚጠጡት እኛን አያገባንም። ግን መጠጥ የሚያመጣው ጠንቅ ሁሉ እሳቸውንም ይጎበኛቸው ነበር። ከትምህርት ቤት እንደወጡ ጊዜ የላቸውም__ የተማሪ ፈተና ሉክ ለማረም ሁሉ። በተለየ አጋጣሚ ፈተና ሉክ የማረም አላፊነት በኔና በአዲስዓለም እጅ ወድቋል። ቲቸር ፍቅሩሰው የተማሪዎችን ፈተና ይሰጡንና መጀመሪያ የኔን እና የአዲስዓለምን ፈተና ሉክ ፈልጋችሁ አውጡ ይሉናል። የኔን ፈተና ሉክ እሱን አርም ይሉታል። የሱን ደሞ እኔን። ይሄንን ካረጋገጡ በኋላ "ዋ ለጓደኞቻችሁ ደሞ ማርክ እንዳጨምሩ" ብለውን መጭ ይላሉ። ታማኝ ነበርን። ውጤታቸውን ቀድመን እንነግራቸዋለን እንጂ ማርክ በፍፁም አንጨምርም ነበር። አንዴ ግን ለሉላዲ ትንሽ ማስተካከያ አርጌ አርሜላታለሁ። የዳሽ ሙላ ጥያቄ ላይ ማይቶካንድሪያ ለሚል መልስ ማይኮታንድሪያ ብላ ፅፋ አስተካክዬ አርሜላታለሁ። ይሄ የሚያስጠይቀኝ ከሆነ አሁን ልቀጣ ዝግጁ ነኝ።
ወደ እዮብ ፋንታሁን እንሂድ። የእዮቤን ፈተና በጥንቃቄ ነው ያረምኩት። በትክክለኛው 52 ከ60 ነው ያመጣው። ባዶ ያልተፃፈበት ፈተና ሉክ ፈለኩ። የእዮቤን እጅ ፅሁፍ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ስሙን ፃፍኩና አዲስ መልስ አዘጋጀቼ 34 ክ60 ሰጠሁት። ፈተና ወረቀቱ አናት ላይ "ፈተና ሉካችን በኪሎ ተሽጧል። ይሄ የሰፈራችን ባለሱቅ ከሽያጭ ተርፎ የሰጠኝ የአንተ ውጤት ነው" ብዬ ፃፍኩበት። እዮቤ ሲበዛ ወሬኛ ነው። እረፍት ሰዓት ላይ ክፍል ተሽሎክሉኬ ገብቼ ፈተና ሉኩን ደብተሩ ውስጥ ከተትኩት። ከረፍት ሲመለስ ሁኔታውን በቅርበት ተከታተለኩት። ፈተናውን አየ ፊቱ ቲማቲም መስሏል። ከ50 በታች ሲያመጣ እዬዬውን የሚስነካው ጎበዝ ተማሪ ነው። ፈተና ወረቀቱን ቦርሳው ጀርባ ደበቀው። በውጤቱ አፍሮ ነው። በአምስተኛው ፔሬድ ስፖርት ስንወጣ ተመልሼ ክፍል ገብቼ ፈተና ሉኩን ወሰድኩት።
በማግስቱ እዮቤ አላስቻለውም የራሱን ውጤት ደብቆ ወሬውን አዳረሰው። "ፈተና ሉካችን በኪሎ ተሽጧል" እያለ። እንደዚህ እንደሚያደርግ በትክክል ገምቼ ነበር። ታድያ "ማስረጃ አምጣ!" ብዬ ቀድሜ የተከራከርኩት እኔ ነበርኩ። አጋጣሚውን ተጥቅሜም ሳያዩ ያመኑ አሽቃባጮችን አንድ ባንድ ሰደብኳቸው። እልሄን ተወጣሁባቸው ነው የሚባለው። እዮቤን ማስረጃ ማስረጃ እያልኩ ሳፋጥጠው አይኑ ፍጥጥ ጥርሱ ግጥጥ አለ። ወሬው ግን አንዴ ካፍ ወቷልና ድሆ ድሆ ዳይሬክተሩ ቢሮ ደረሰ።
በሶስተኛው ቀን ቲቸር ፍቅሩሰው ፈተና ሉካችንን ይዘው ከች አሉ። እዮቤን ስከታተለው ነበር። 52 ከ60 ያመጣበት ፈተና ሉኩ ሲደርሰው ውሃ ነው የሆነው። ሁላችንም ፈተና ሉካችንን ከተረከብን በኋላ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እና የትምህርት ቤቱ ሁነኛ ገራፊ ቲቸር ባንተአምላክ ያንን እባብ ጎማቸውን እያወዛወዙ ተከታትለው ገቡ። ተማሪዎች የፈጠራ ወሬ ማውራት እንድሌለብን በብዙ በብዙ ከመከሩን በኋላ እዮቤ መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ወደፊት እንዲወጣ ተደረገ። ሱሪውን አውልቆ ዴስክ ላይ ተጋደመ። ከዛ በኋላ ያለውን ድምፁን እንጂ ሁኔታውን በአይኔ መከታተል አልቻልኩም። ይሰቀጥጥ ነበር።
እዮብ ፋንታሁን አሁን ሰነድ ማረጋገጫ ቢሮ ውስጥ ሁነኛ ሰው ሆኗል። አጋነው ሲያወሩለት 'እውነተኛ ሰነድና ፎርጂድ በሽታ ሁሉ ይለያል' ይላሉ። መቼስ ግሩም ነው ይሄ። እዮቤ ይሄንን ከ25 አመት በኋላ የምነግርህ ምን ያህል ጠቃሚ ትምህርት እንዳስጭብጥኩህ ተገንዝበህ እንድታመሰግነኝ ነው። አየህ አንተ እኮ ያኔ የራስህን ፅሁፍ እንኳ ሌላ ሰው ፅፎ ሲሰጥህ አምነህ የምትቀበል እንከፍ ነበርክ። አየህ እንዴት ስል እንዳረኩህ? ቀበቶ ለመፍታትም የዘገየ ራሱን የሚቆጣጠር ሰው ነው ሲሉህ ሰሰማ... ይሄስ የማን ውጤት ይመስልሃል? አየህ ምን ያህል ታማኝ እንዳረኩህ? በል ምስጋናውን ወዲህ በል ሃሃሃሃ
በፀሎት አረፋይኔ
በፂ የሉላዲ የቅርብ ሰው ከመሆኗ ባሻገር የቁምላቸው ጠላቱ ነበረች። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ብዙ ጊዜ አይግባቡም ነበር። ብዙ ጊዜ እሱ ሲያመናጭቃት ሲሰድባት እሷ ደሞ ስትሸሸው አይም ነበር። ብቻ በምን ቀን ኮከባቸው እንደገጠመ ባላውቅም አንድ ቀን አንድ ጠቃሚ መረጃ ለቁምላቸው ትነግረዋለች። ጠቃሚነቱ ደግሞ ለሱ ነው።
የኔን የግል እንግሊዘኛ መፅሃፍ መጥፋቱን የነገርኩት ለሉላደይ ብቻ ነበር። ለእዮብ እንኳ አልነገርኩትም። ሉላደይ ለበፀሎት ከምን ተነስታ እንደነገረቻት አላውቅም። የማውቀው ግን የነገረቻት በቀናነት መሆኑን ብቻ ነው። በፂም የዋህም ቀናም ነች። የመፅሃፍ መጥፋት ታሪክም ለማንም የምትነግረው ተራ ነገር ነው። ግን በበፀሎት አማካኝነት ቁምላቸው ታሪኩን ሲሰማ ታሪኩን ከተራነት ወደ ሌላ ነገር ቀየረው። በኋላ እናዳጣራሁት ከሆነ በፀሎት የነገረችው በየዋህነት ነበር። እኔና ቁምላቸው የምንቀራረብ ስለሚመስላት (በጣም የምንቀራረብ አርጎ ሲያወራላት ስለነበር) ራሱ ይነግረዋል አይነግረውም የሚለውን ለማጣራት ድንገት ያነሳችው ወሬ ነበር። ቁምላቸው ግን ከፉ ነውና ወሬውን ለክፋቱ ተጠቀመበት። የሉላደይን መፅሃፍ ሰረቀ ቢባል በተለይ ሉላደይ ታምናለች ብሎ ተነሳ። ከዚ በኋላ ነው ቁምላቸው ብርጌድን አቋቁሞ ወደ ተግባር የገባው።
ቅጣት___
ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም። ስቀልድ ነው በፂዬ አንቺን እንዴት እቀጣለሁ? የሉላዲ ጉደኛ ከመሆንሽም በላይ ለየዋህነትሽ ከኔ በላይ ምስክር አልሻም። ግን በምንም ምክንያት ወሬው ቀለለም ከበደም ጓደኛሽ ሰው ነገረኝ ብላ የነገርችሽን ነገር በምንም ምክንያት በምንም መልኩ ለሌላ ሰው አይነገርም። ወሬው ምንም ሆን ምንም ሉላዲ በመወራቱ ቅር ስላላት እኔም ቅር ብሎኛል። ስለዚህ ይሄ ነገር አሁን ድረስ አድጎብሽ ከሆነ ተይ እሺ! ቀጥቼ ባስተምርሽ ይሻል ነበር? ፃፊልኝ ሃሃሃሃ
ጀሚል አህመድ
ጀሚልም ሁለተኛ የቅርቤ ሰው ነው። አብረን ሚኒሚድያ እንሰራለን። ምን ዓይነት ወሬ አፌን እንደሚያስከፍተኝ በሚገባ ያውቅል። በወቅቱ አማርኛ አስተማሪያችን ለታዋቂ ሰው ደብዳቤ ፃፉ ብለውን ነበር። እኔ ደሞ ልፅፍ ያሰብኩት ለዚነዲን ዚዳን ዚዙ ነበር። ጀሚል ሚኒሚድያ ውስጥ የስፖርት ክፍል አዘጋጅ ስለነበር ስለዚዳን አንዳንድ መረጃ ይሰጠኝ የነበረው እሱ ነው። ከእዮብ ፋንታሁን ጋር ተነጋግረው መፅሃፍ ሰረቀ የተባልኩ ቀን ጉድ አደረጉኝ።
ከትምህርት ወጥተን ወደ ቤት እየሄድን እያለ ጀሚል ሰለዚዳን ቤተሰቦች አዲስ መረጃ ያወራልኝ ጀመር። እንደለመደብኝ አፌን ከፍቼ ማዳመጥ ጀመርኩ። ሉላዲን ቀድሜ አልፊያት ስሄድ እንኳ ልብ አላልኩም ነበር። በዚህ መሃል ሌላ ችግሬን የሚያውቀው እዮብ ፋንታሁን የሉላዲን እንግሊዘኛ መፅሃፍ በእጄ አስጨበጠኝ። እንዴት እንደተቀናጁብኝ አሁን ድረስ ባሰብኩት ቁጥር ይገርመኛል። እንዲህ ከሆነ በኋላ ነው "ሌባ ሌባ ሌባ ... " የሚል ድምፅ ከተመስጦዬ ያነቃኝ።
ቅጣት 3
ጀሚል አህመድ አብሮኝ ሚኒሚድያ ይሰራል። የስፖርት ክፍልም አዘጋጅ ነው። በወቅቱ ትምህርት ቤታችን ሁላችንም በቀለም ተከፋፍለን የየራሳችን ቡድን ነበረን። ነጭ፣ ሰማያዊ፣ ቀይ፣ ሐምራዊ ... የመሳሰሉት። እያንዳንዱ ተማሪ የየራሱ ቡድን አለው። እኔ ለምሳሌ የሐምራዊ ቡድን አባል ነበርኩ። ለሐምራዊ ቡድን ለመጫወት ባልመረጥ እንኳ ሐምራዊን የመደገፍ ግን የውዴታ ግዴታ አለብኝ። ጀሚል ደሞ የነጭ ቡድን አባል ነበር። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ የነጭ ስብስብ አባላት በእድሜ ትንሽ ከፍ ያሉና ኳስ የሚችሉ ልጆች ስብስብ ሆኖ ነበር። እና ጀሚሌ ደርሳ ለኳስ ምረጡኝ ስትል በአንድ ድምፅ ነው "ስለ ኳስ ማውራትና መጫወት ይለያያል" ብለው ፂሟን አብርረው ያበረሯት። በርግጥ ያኔ ፂም አልጀመረውም። እና በጣም ተበሳጨ። የነጭ ስብስብ አባል ቢሆንም የነጮችን ጨዋታ ፈፅሞ ላለማየት ለራሱ ቃል ገባ።
የሚኒሚድያ ስራው ስለስፖርት መዘገብም ስለነበር ነጮች ኳስ ያላቸው ቀን አንድ የሰፈሩን ልጅ ወጤቱን እንዲነግረው ወክሎ እሱ ከሰፈሩ ልጆች ጋር ኳስ ሲራገጥ ያመሻል። ያ የተወከለ የሰፈሩ ልጅ ደሞ የትምህርት ቤታችን ተማሪ አልነበርም። ግጥሚያው ያለው ከ9፡30 በኋላ ስለነበር ተመልካች ከውጪ መግባትም ይችል ነበር።
በአንድ የነጮች ግጥሚያ ቀን የጀሚልን የሰፈር ጓደኛ ተጠግቼው ቁጭ አልኩ። አያውቀኝም። ቀድሜ ያዘጋጀሁትን ወረቀት ሰጠሁት። የስፖርት ዜና ሪፖርት ነው። ሌላ ጊዜ ሚኒሚድያ ላይ የሚቀርበው ቢጫ ቀይን 3 ለ 1 አሸነፈ ምናምን ብቻ ተብሎ ነው። ሌላ ማብራሪያ ቀርቦ አያውቅም። እኔ ያዘጋጀሁት ወረቀት ግን ራዲዮ ላይ እንደምሰማው የተብራራ ነገር ነበረው። የጀሚል ጓደኛ የሰጠሁትን ወረቀት ካነበበ በኋላ ደስ አለው። ዜናው ባጭሩ ነጮች በሰማያዊ 4 ለ 2 መሸነፋቸውን ይገልፃል። የትምህርት ቤታችን ጉልቤ ሙሉጌታ ታደሰ ኢሊጎሬ እንደሳተ ተገልጧል። "ኳሱን ወደ ላይ ዛቀው" ተብሎ። ሌላው ሁለተኛ የትምህርት ቤታችን ጉልቤና ግዙፉ የነጮች በረኛ አኗር አብዱላዚዝ ነው። ዜናው ላው ላይ አኗር ላይ 2 ጎል በሎጬ እንደገባበት ተካቷል። የሰማያዊው አጥቂ አሉላ ተስፋዝጊ 2 ጊዜ አኗርን አሸናው ተብሎ።
የጀሚል የሰፈር ጓደኛ በወሬ መሃል እየተካሄደ ያለውን ዋናውን ጫወታ ረስቶት ነበር። ጨዋታው ካለቀ በኋላ የሰጠሁትን ወረቀት እያሳየኝ "ይሄ የዚህ ጨዋታ ውጤት ነው ወይ?" ሲለኝ የደነገጥኩትን ድንጋጤ አሁን ድረስ አረሳውም። "አዎ እኔ ቀድሜ ገምቼ ነው፤ ቆይ ትንሽ ላስተካክለው" ብዬ ወረቀቱን ተቀብዬው ትንሽ አቆይቼ ስሰጠው "እኔን ነኝ የፃፍኩት ልበለው ወይ?" ብቻ ነው ያለኝ። "እንዴታ!" ስለው እጅግ አመስግኖኝ ሄደ። ቆይቶ ሲመለስ በድጋሚ ደነገጥኩ። "ስምህ ማነው?" ሲለኝ "እዮብ ፋንታሁን ነኝ" ካልኩት በኋላ ነው የተረጋጋሁት።
ጀሚሌ ዜናውን አሻሽሎ ተራቆበት መጣ። የጠዋት ዜና አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ ለስፖርት ዜናዎች ጀሚል አህመድ ብዬ ማይክራፎኑን ሰጠሁት። ጀሚል ዜናውን ሲያነብ የሚኒሚድያው አላፊ ባግራሞት ሲያዩት ነበር። የተማሪዎች ሰልፍ ላይ ግን ከባድ ሁካታና ረብሻ ተነስቶ ነበር። ነጭች ጨዋታውን 2 ለ ባዶ አሸንፈው ሳለ 4 ለ 2 ተሸነፉ ተብሎ መዘገቡ ነጮች ብቻ ሳይሆኑ ተሸናፊዎቹ ሰማያዊዎችም አብረው ተንጫጩ። በኋላ እንደሰማሁት ጉልቤዎቹ ሙሉጌታና አኗር ሰልፉ ላይ የሚይዙት የሚጨብጡት አተው ነበር።
የሚኒሚድያው አላፊ ሁኔታውን ከኔ ካጣሩ በኋላ በህይወቴ ደግሜ ላየው የማልችለው አይነት የኩርኩም አይነት አናቱ ላይ አሳረፉበት። ቆይተው ግን የሰራው ስህተት እንዳለ ሆኖ ዜና አፃፃፉን ግን እንደወደዱለት ፀጉሩን እያሻሹ ነገሩት። ኩርኩሙን ረስቶ ሲደሳሰት በአንክሮ እከታተላለሁ። ጭራሽ አጥቂው ሙሉጌታንና በረኛው አኗርን ፈፅሞ ረስቷቸዋል።
ትምህርት እንዳለቀ እሳትና ጭድ የሆኑት ጉልቤዎቹ አኗርና ሙሉጌታን አብረው አየዋቸው። ጀሚል ወደ ሰፈሩ ሲሄድ ከኋላ ከኋላ ይከተሉታል። እኔም ከርቀት እየተከተልኳቸው ነው። የጀሚል ሰፈር መግቢያ ቀጭኗ መንገድ ጋር ሲደርስ ሮጠው ተጠጉት። በረኛው አኗር ተንደርድሮ ቀለበው። አጥቂው ሙሉጌታ በርግጫ በረኛው አኗር በጡጫ ተቀባበሉት። ሙሉጌታ ይጠልዛል አኗር በቦክስ ያወጣዋል። እንዳይሞት እንዳይሽር አርገው ከንተውት ደም በደም ሲሆንባቸው ጥለውት ሄዱ። በኋላ አንድ ነገር ቢሆን ፀፀቱን አልችለውም ብዬ ደግፌ ቤቱ አደረስኩት። ለዚ ውለታዬ አንድ አመት ሙሉ ጮርናቄና ፓስቲ በፍቅር ጋብዞኛል።
ጀሚል አሁን እሳት የላሰ የስፖርት ጋዜጠኛ ሆኗል። ቅድመ ግምቱና ከጨዋታ በኋላ ያለው ትንታኔ በብዛት ይወደድለታል። ብዙ አድማጭም አለው። እንደ አንዳንድ ተንታኞች የጨዋታ ሃይላይት እና ስታት አይቶ ሙሉ ጨዋታውን እንዳየ አርጎ አይከትፍም። በተመሳሳይ ሰዓት ሁለት ጨዋታ ሲኖር እንኳ ሁለቱንም ሙሉውን አይቶ ነው የሚተነትነው። ይሄ ታማኝነት አፍርቶለታል።
ጀሚሌ ይሄን ከ25 አመት በኋላ የምነግርህ አንድ ምን ያህል እንደቀረፅኩህ እንዲገባህ ነው። አንድም ጥያቄ ልጠይቅህ ነው። ሌሎቹን አመስግኑኝ ብዬ ካንተ ምስጋና ያልፈለኩት ቀድመህ በጮርናቄና ፓስቲ ስለከፈልከኝ ነው። አንደኛ ጥያቄዬ "ከቁምላቸው ጋር ለመተባበር ምን ያህል ተከፍሎህ ነው? ካልተከፈለህ ደግሞ ምን አነሳሳህ? መረጃው የለኝም"። ሁለተኛ ጥያቄዬ ደሞ "ያን የሰፈርህን ልጅ ምን አረከው?" ነው ... "ስለ እዮብስ ነግሮህ ይሆን?" ሃሃሃ
ተደራራቢ ኳስ ያለ ቀን ሙሉ ኳሱን አይተህ አይንህ አብጦ ሳይህ አኗርና ሙሉጌታ አይኑን አሳብጠው ምን አይነት ጠቃሚ ነገር አስጨበጡት እያልኩ እደመማለሁ። ብቻ በርታ ሃሃሃ
ቁምላቸው ግርማ
ከቁምላቸው ጋር ፀብም ዝድናም የለንም። ቁምላቸው 16 አመቱ ነው። ወይ 17። እኔ ደሞ በ12 እና 13 መሃል ያለው ሁጫጭ ነኝ። ቁምላቸው ሉላደይን እንደሚወዳት ይሰማኛል። መብቱ ነው አልቃወምም። እኔ ሉላደይን እወዳታለሁ? አላውቅም! ብቻ የ12\13 አመት ልጅ ወደድኩ ከሚለው በላይ ግን ትሰማኛለች። የተለዩ የተለዩ ብዙ ብዙ ነገሮች መሰማት የጀመሩኝ በሷ ነው። ይሄን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው ስለምናወራ ወደ ቁምላቸው እንሂድ ...
ጓደኞቼን እንዴት እንደቀጣው ያየ ሰው ቁምላቸውን ደሞ ምን አይነት አደገኛ ቅጣት ይቀጣዋል ብሎ እንደሚገምት አልጠራጠርም። ግን ሰው ቢያምነኝ ይመነኝ ባያምነኝም ብዙ አልገረምም እዚህ ድረስ ቁምላቸውን ምንም አይነት ቅጣት ለመቅጣት አላሰብኩም ነበር። ምክንያቱም ቁምላቸው ጓደኛዬ አይደለም። እሱ ለኔ በጣም የሩቅ ሰው ነው። ልክ ባይሆንም ደሞ ሉላደይ የምትብላ ምክንያት ነበረችው። አዝኜ የነበረው በጓደኞቼ ላይ ነበር። እነሱን የእጃቸውን ከሰጠው በኋላ እሱን ረስቼው መኖር ጀመርኩ።
ቁምላቸው ግን ሊተወኝ አልቻለም። በወቅቱ ሰፈራችን ቀለበት መንገድ እየተሰራ ነበር። ከአስፋልቱ ላይ የሚቆፈረው አፈር ደሞ የሚደፋው ቴክሳስ ገደል የተባለ ልዩ ቦታ ነበር። አፈሩን ከአስፋልቱ ላይ ጭነው ወደ ቴክሳስ ወስደው የሚደፉት መኪኖች ደሞ የሚሄዱት ቀስ ብለው ስለሆነ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የምሄደው በነሱ ላይ ተንጠልጥዬ ነው። አንድ ቀን እንደተለመደው ተንጠልጥዬ ወደ ቤቴ ስሄድ ከኋላዬ የሚሮጥ ኮቴ ሰማሁ። ሌላ የሚንጠለጠል ሰው ነው ብዬ ቦታ ለመልቀቅ ወደ ዳር ተጠጋሁ። መንገዱን በሙሉ አቧራ ስለሚቦን በቅርብ ካልሆነ በቀር ምንም መለየት አይቻልም። እኔ ራሱ ማንም ሰው መንጠልጠሌን ስለማይለይ ነው ሰፈር ድረስ በድፍረት የምሄደው። ያ የሚሮጥ ኮቴ ቀረበኝ። ጀርባዬን ሲይዘኝ መንጠልጠል አስቦ በስህተት የያዘኝ ነው የመሰለኝ። በደመነፍስ መኪናውን ላለመልቀቅ እታገላለሁ። በመጨራሻ ወደኩኝ። ረጅም ሰአት መንገዱ ላይ በሆዴ ተስቤ ስለነበር ከግራ አይኔ በላይና በታች ረዥም ጊዜ የቆየ ጠባሳ ነበረብኝ። ማስታወሻው የሚኒስትሪ ፎቶዬ ላይ አለ። በግራ ጎኔ አንድ አጥንቴ ወደ ውስጥ ገብቷል። እድለኛ ሆኜ ነው ከኋላዬ ሌላ መኪና ያልነበረው።
ያ እጅ ግን የቁምላቸው መሆኑን ያወኩት ከወር በኋላ ነበር። ናትናኤል የሚባል የሰፈር ጓደኛዬ እህቱ ቤቷ ድረስ ጠራቺኝ። የሆነውን ራሱ የነገራትን ነገረቺኝና ቁምላቸውን በጣም እንድጠነቀቀው መከረቺኝ። ቁምላቸው እሷንም ያስቸግራት ስለነበር በጣም እንድትፈራው ብሎ የነገራት ይመስለኛል። እሷ 11ኛ ክፍል ተማሪ ነች። ከዛ በፊት ያደረገኝንም መልሼ ያደረኩትንም ልቅም አድርጌ ነገርኳት። ከዚህ በኋላ ግን እሱን የምቀጣው ቅጣት ሰቅጣጭ እንደሚሆን ነግሪያት ተለያየን።
ያኔ ከመኪና ላይ ወድቄ የነበረ ጊዜ ሶስት ሳምንት ትምህርት ቤት አልሄድኩም ነበር። ታድያ አንድ ቀን ቤተሰብ ጎረቤት ተሰብስቦ ቡና የሚጠጣ ሰአት ላይ ስልክ ተደወለ። ሴት ነች ደዋይዋ። ተፈላጊው ደሞ እኔ ነኝ። ሁሉም ቡና ጠጪ አይኑ ሁሉ እኔ ላይ ሰፈረ። ልጅቷን ባንቃት ሁሉ ደስ ይለኝ ነበር። ገና "ሄሎ" ስል ደዋይዋ ሉላደይ ሆና ተገኘች። እንዴት ልጠምጠምባት? ስልክ ሆነብኝ። እጅግ ናፍቃኝ ነበር። ለደቂቃ ባለቡናዎቹን ረስቻቸው ነበር። ትዝ ሲለኝ ወሬው የዘላለም ነው። ወደ ቀልቤ ተመለስኩ።
ሉላደይ ታወራለች... እንዴት ነህ? ምን ሆነህ ነው? የመሳሰሉትን ቶሎ ቶሎ ትጠይቀኛለች። መልሴ ሌላ ሌላ ሲሆንባት ጊዜ ሁኔታው ገባት። "ከወንድምሽ እገለብጣለሁ" ያልኳት ከመሬት ተነስቼ ነበር። ወንድሟ እኮ 6ኛ ክፍል ነው። ለቡና ጠጪዎቹ የጓደኛዬ እህት ነች ማለት ፈልጌ ነው። ወዲያው ጨዋታውን ከረበተችው። "ወንድሜ ታድፖል እንዲያመጣ ታዟል። የናንተ ሰፈር ወንዝ ምኑ ጋር ነው?" ስትለኝ እንዴት አቅፌ ልሳማት። ስልክ ሆነብኝ። የበለጠ ወደድኳት። ሉላዲ ትለያለች የምለው እኮ ለዚ ነው።
ቡና ጠጪዎቹ ምናልባት ታድፖል ካልገባቸው ብዬ "የእንቁራሪት ልጅ ዓሳ የሚመስለው የሚገኘው አቡዬ ፀበል በታች ያለው ወንዝ ውስጥ ነው። ወንድምሽ በትልቅ ብርጭቆ ውሃ አርጎ ታድፖሉን ይያዝና ይክተተው። ውስጡ ለምግብ ትንሽ አሸዋ ይጨምርበት"። ቡና ጠጪዎቹ ወሬው ትምህርታዊ እና እንቁራሪታዊ ሲሆንባቸው ወደ ቀደመው ወጋቸው ተመለሱ። እፎይ አልኩ። ያን ቀን ግን የተሰማኝን ደስታ መቼም አረሳውም። ማታ ከነጫማዬ ነው እንቅልፍ የወሰደኝ።
የሉላደይን የመደወል ወሬ ለብቻዬ ልይዘው አልተቻለኝም። ከእዮብ የሚቀርበኝ የለምና (ከቅጣቱ በኋላ ጓደኝነታችንም ከልብ ቀጥሎ ነበር) ቤቱ ድረስ ሄጄ ነገርኩት። የእዮቤ ሱስ የማይለቅ ነውና እኔ ትምህርት ቤት ከመመለሴ በፊት ወሬውን ቀድሞ አድርሶ ጠበቀኝ። ሉላደይም ቁምላቸውም ሰሙ። ትምህርት እንደገባው ሉላዲ ቅር ያላት መስሎኝ ይቅርታ ስላት። "እንዴ ለምን? እንደውም በጣም ነው ደስ ያለኝ" ብላ ግራ ጆሮዬን ጫፍ እጅግ ስነካው ደስ በሚለኝ ጣቷ ቆንጠጥ አረገቺኝ። በምትወደው ሰው እጅግ በምትወደው ጣት በስሱ መቆንጠጥ ያለውን ስሜት የደረሰበት ብቻ ነው የሚያውቀው። ያኔ በግራ ጆሮዬ በኩል ሲወሩ የሰማኋቸውን ወሬዎች ዛሬ ድረስ ቃል በቃል አስታውሳቸኋለሁ። ደጋግሜ እሷ እንዳረገቺኝ ጆሮዬን ስቆነጥጥ ስለነብር ያን ቀን ጆሮዬ በጣም ቀልቶ ነበር። እንዳመጣብኝ ከነጫማዬ ተኛው።
በሳምንቱ ቁምላቸው ምንም እንዳልተፈጠረ መጣና የነ ሉላደይን ስልክ ስጠኝ አለኝ። አጠያየቁ እጅግ የፀባይኛ ሰው ነውና አሳዝኖኝ የነ ናትናኤልን ስልክ የነ ሉላደይ ነው ብዬ ሰጠሁት። የሚደውልበትንም ሰአት አስጠንቅቄ አስጠናሁት። መክሰሴን በልቼ እነ ናትናኤል ቤት የምደርስበትን ሰአት ነው የነገርኩት። የነ ናትናኤል ቤት ደሞ በዛ ሰአት ከሱና ከእህቱ ሰብለ ውጪ ማንም አይኖርም። ቁምላቸው ከመደሰቱ የተነሳ አቅፎ ወደ ላይ ካነሳኝ በኋላ 100 ብር ___ ድፍን 100 ብር አውጥቶ ሰጠኝ። በጣም ተደስቼ ፌንት የምበላ መስሎት ሁሉ ነበር። "ያንሳል!" ስለው ራሱ ፌንት ከመብላት ለጥቂት ነው የተረፈው። እየገረመው በማግስቱ እንደሚጨምርልኝ ነግሮኝ ሄደ። ቁምላቸው በሉላዲ ጉዳይ ሳይሆን ከመኪና ላይ ስቦ በጣላኝ በገንዘብ የቀጣሁት ቅጣቱ ነው። በተለያየ ሰበብ 4 መቶ 25 ብር ተረክቤዋለሁ። ዋናውን ቅጣትን ግን ገና አልቀጣሁትም።
ሰብለ ሀብተማርያም
ሰብለ የሰፈር ጓደኛዬ ናትናኤል እህት ነች። ከኛ በእድሜ ስለምትበልጥና ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ተማሪ ስለሆነች ብዙ ነገር ታውቃለች። የቁምላቸውን የስልክ ጉዳይ ስነግራት መጀምሪያ ተቆጣቺኝ። ቆይተን እኔና ወንድሟ ስንለምናት ጊዜ እሷም ትንሽ ውጤቱን ለማየት ጓጓች። 'ቁማላቸው በናንተ ስልክ ሉላደይን ፈልጎ ሲደውል አንቺ ሉላደይ ነኝ ብለሽ አናግሪው' ነበር ሃሳባችን። ሁለት ቀን አልደወለም። አርብ ለት ግን ልክ ባልኩት ሰአት ላይ ስልኩ ጠራ። ጆሮዬ እንደዛ ቆሞ አያውቅም። "አዎ ሉላደይ ነኝ" ስትል እኔና ናቲ ተቃቅፈን መጨፈር ጀመርን። ረጅም ሰአት ዝምብላ ሰማችውና "እሺ ቻዎ" ብላ ዘጋቺውና "ይሄ ዲያቢሎስ ነው በስማብ" ብላ ወደ ጓዳ ገባች። ተከትለን ምን እንዳላት እንድትነግረን ብንለምናት የመጨረሻ ገገመች። ምንም አልመሰለኝም ዋናው መደወል መጀመሩ ነው ብዬ በደስታ ወደ ቤቴ አመራሁ።
በማግስቱ ቅዳሜ ናቲ ሳይኖር ሰብለ ቤት አስጠራጪኝ። ግራ ገባኝ። ወንድሟ ስለሌለ ወሬው እኔን ብቻ እንደሚመለከት በስሱ ገብቶኛል። "አንተ በጣም ተጠንቀቀው ቁምላቸው በጣም መጥፎ ሰው ነው" ብላ ጀመረች። የማውቀው ጉዳይ ስለሆነ አልገረመኝም። በስልክ ያወራውን ነገረቺኝ። ማንነቱን አልተናገረም። ያወራው ግን ስለኔ ነበር። "አጠገብሽ የሚቀመጠው ሌባው ልጅ..." እያለ። ሰብለ የሰፈሬ ሰው ስለሆነች ጠንቅቃ ስለምታውቀኝ እንጂ ወሬውን ቀጥታ የሰማቺው ሉላደይ ብትሆን ኖሮ በጣም ትወዛገብ እንደነበር እገምታለሁ። እጅግ ነው የደነገጥኩት። ወሬው እንኳን እዚ ሊወራ ደግሞ የሚታሰብ አይደለም። "እውነትም ዲያብሎስ!" አልኩ አፌን ከፍቼ።
"እና ምን አሰብክ?" ስትለኝ ነው ከሃሳብ የተመለስኩት። ስለ ቅጣቱ መስሎኝ ሉላደይ ቀጠረችህ ብዬው እንደማይቻል ባቅም አንበሳ ግቢ ቀጥሬው አንበሳ ሁሉ ላስበላው እያሰብኩ እንደሆነ ነገርኳት። ይሄን ያህል ነው እየተዘጋጀሁለት የነበረው። ሰብለ ግን ሌላ ወሬ ማውራት ጀመረች.... "አየህ አንተ የምታውቀው የመፅሃፍ ሌባ እንዳስባለህ ብቻ ነው። ከመኪና ላይ የጣለህንና በስልክ ያወራውን እኔ ባልነግርህ ኖሮ ጭራሽ አታውቅም ነበር። ስለዚህ ሰው ላረገብህ በሙሉ ተበቅለህ አትችለውም። ምክንያቱም ሰው የሚያረግብህን በሙሉ ማወቅ አትችልምና ነው። ሰው የሚያረግብህን ግን በስውር የሚያይ የሰማይ አምላክ አለ። እሱ ካመንከው ይበቀልልሃል። በቀል የእግዚሃብሄር ነው!" ብላ ፊቴን መሸሽ ጀመረች። ፊቴ መለወጥ እየጀምረ ነበር።
"አረ ባክሽ... " ብያት ስነሳ "አንተን ራሱ ጓደኞችህን ማን ቀጪ አረገህ? እንደውም በዚህ ስራህ ራስህ ትቀጣለህ!" ስትለኝ እጅግ በጣም ነው የተናደድኩት። አበድኩ ነው የሚባለው። ለፈለፍኩ። አየሽ ሰረቀ የተባለው እኮ የሉላደይን መፅሃፍ ነው... ሌባ የተባልኩት እኮ በሉላደይ ፊት ነው... ሉላደይ ሉላደይ ሉላደይ ብዙ ሉላደይ ደረደርኩ። ያን ቀን እግዜር ሲተፋኝ ከክፍል አርፍደን ወጣን እንጂ ሙሉ ትምህርት ቤቱ ሌባ ይለኝ ነበር እኮ። ብዙ ለፈለፍኩ። እንባዬ ከየት እንደመጣ አላውቅም ዘረገፍኩት። እንደ እብድ ከቤቱ እየለፈለፍኩ ስወጣና ጋሽ ሀብተማርያም ሲገቡ አንድ ሆነ። ወደ ቤት መልሰው ይዘውኝ ገቡ።
እኔ ማውራት አልቻልኩም። ሰብለ የሆነውን ተረጋግታ አንድ በአንድ አወራችልኝ። ሁኔታዋ ቀድማ የወቀሰቺኝ አትመስልም። እጅግ እንደተበደልኩ አርጋ ነው ያወራችው። ጓደኞቼን የቀጣሁትን ቅጣት የተቀበለቺው ነው የሚመስለው። ተረጋጋሁ። ጋሽ ሃብቴ ሁኔታውን በትህግስት እና ጥንቃቄ ከሰሙ በኋላ መረጋጋቴን ሲያዩ ለነገ ቀጥረው አሰናበቱኝ።
ጋሽ ሀብተማርያም
በማግስቱ ንዴቴም ለቆኛል ጋሽ ሀብቴም ሲያወሩ ደስ ስለሚሉ ተረጋግቼ ነው ቤታቸው የሄድኩት። እንደ ትልቅ ሰው ፊለፊታቸው ወንበር ስቤ እንድቀመጥ ሲያደርጉ ገርሞኝም ደንግጬም ነበር። በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ሰው የመሆን ስሜት ተሰማኝ። በርጋታ ማውራት ጀመሩ። ሁሉ ነገር አውቀው ነበር። ስለ እዮብ፣ ስለ ሰብስቤ፣ ስለ ጀሚል ስም ሳይሳሳቱ ሲያወሩ ጓደኛዬ እየመሰሉኝ መጡ። በኋላ ጥሩ ሄደው ሄደው የልጃቸውን የሰብለን ተግሳፅ ደገሙልኝ። "አንተን ማን ቀጪ አረገህ?" ሲሉኝ በሳቸው ውስጥ ሰብለን ማየት ጀመርኩ። እውነት ለመናገር በዚህ አባባላቸው ተናድጃለሁ። ግን በሰብለ እንደተበሳጨሁት አልሆንኩም።
ጥቂት ዝም ብዬ ቆየሁና "እና ዝም ማለት ነበረብኝ?" አልኳቸው። ፊቴን በደንብ ካጤኑት በኋላ "አይደለም። ዝም ማለትማ አልነበረብህም። በጭራሽ! መቀጣትም አለባቸው። ግን አንተ ቀጪ አይደለህም ነው ነጥቡ" ብለው አከሉልኝ። በሆዴ 'እና ማን ነው ቀጪው?' እያልኩ ሳሰላስል ቀጠሉ "አየህ አንተ በግል እንደ ወላጅ እንደቀጣሃቸው ነው የሚሰማህ። አንድ ልጆቹ ሁሉ እንደተቀጡም ማን እንደቀጣቸውም አላወቁም። ሁለት ለምን እንደተቀጡም አላወቁም። እና ይሄ ሊያስተምራቸው አይችልም። አንተ የያዝከው በቀል ነው። በቀል ደሞ አንተንም እነሱንም ማንንም አይጠቅምም... " አላስጨርስኳቸውም "ስለዚህ ዝም ማለት ነበረብኝ?" ሳላውቀው ተኮሳትሪያለሁ። ፈገግ ብለው በርቀት ፀጉሬን ነካ አርገው "እልህህ ጥሩ ነው የሚጠቅም ነገር ላይ ካዋልከው..." ትንሽ ትንፋሽ ወሰዱና "መሆን የነበረብት እነሱም ተቀጥተው ሌሎች ተማሪዎችም ከነዚ ተማሪዎች ጥፋት መማር ነበረባቸው" ሲሉኝ ያደረኩትን በአደባባይ ተናገር ያሉኝ መስሎኝ በሆዴ 'ጋሽ ሀብቴ ምን ነካቸው?' እያልኩ ሳስብ ...
"አየህ ጉዳዩን ትምህርት ቤት ለአስተማሪ ብትናገር ኖሮ ... የሰሩት ስራ የልጅ ስላልነበረ አስተማሪዎቻቹ በደንብ ይቀጧቸው ነበር። ሌላው ተማሪም በነሱ ቅጣት ይማር ነበር። ከሁሉ በላይ ደሞ አንተም ነፃ ትወጣ ነበር። እስካሁን በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ ሌባ ተደርገህ መሳል እኮ አልቀረልህም።" እዚህ ድረስ አዕምሮዬ ይሄን ባለማሰቡ ገረመኝ። የምታስጨንቀኝ ሉላደይ ነበረች። ለሷ ወድያው ያልነገርኩበትም ምክንያት ነበረኝ። ሌላው ግን ሌባ መሰልኩት አልመስልኩት ግድ አልሰጠኝም መሰለኝ። ወይም ፍቅርና በቀል አውሮኝ ይሆናል። እኔ እንጃ!
ከብዙ ብዙ ምክር ጋር ቁምላቸውን እንድተወው ነገሩኝ። ሰንበት ትምህርት ቤት ገብቼም ብዙ መማር ያለብኝ ነገር እንዳለ አስረድተው ምሳ ጋብዘው አመስግነው ወደ ቤቴ ላኩኝ። የሰንበቱን ብስማም ቁምላቸውን መቅጣት መተዉን ግን ፈፅሞ አልተቀበልኩትም ነበር።
የቁምላቸው ቅጣት
ቁምላቸውን ልቀጣ የማስበው የትኛውም ሃሳብ አላረካ ሲለኝ ሳወጣ ሳወርድ ሳልፈልግ ብዙ ቆየሁ።በዚህ መሃል ከነ ሰብለ ጋር በሰንበት ያለኝ ግንኙነት እየጨመረ መጣ። ሳላውቀው እየላላሁ መጣሁ። እንደ ንፁህ ሰው ምክር ሰምቼ መቅጣቱን ተውኩት ብዬ አልዋሽም። ሳላውቀው በጊዜ ሂደት ግን ቢቀርስ የሚል ሃሳብ ሽው እያለብኝ መምጣት ጀመረ። መጀመሪያውኑም የሚያረካኝ በቀል አጥቼለት ነበር። በኋላ እየቆየሁ 'ቁምላቸው ለምንድነው እንደዚህ መጥፎ ሰው የሆነው?' የሚለውን ማሰብ እንደጀመርኩ ሰሞን ሚኒስትሪ በጣም የመዳረሱ ደወል ተደወለ። በቃ ሁለት እግሩን ይብላ ብዬ ተውኩት።
ከዛ ረሳሁት ረሳሁት። 9ኛ ክፍል የተለያየ ትምህርት ቤት ገባን። ከዛ ወዲህ 25 አመት ሙሉ አይቼውም ስለሱ ሰምቼም አላውቅም። ማንም ይቅጣው ማንም ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ አውቃለሁ። እውነት ለመናገር ስለ እኔ ረስቼው ነበር። አንድ ቀን ስንኳ ክፉ እንዲሆንበት ተመኝቼም አላውቅም። ግን ያለበት በሽታ በተለይ ለሴቶች ያለው ጥላቻ ካልታረመ በቀር የሆነ ቦታ ላይ እንደሚጥለው እገምታለሁ። በሰብለና በበፀሎት እንደተረዳሁት ከሆነ ሴቶችን የሚቀርበው ሊጎዳቸው ስለሚፈልግ ነው። ለሉላዲ እኔ ፈንጅ አጥሯ ሆኜላት እንጂ አይቀርላትም ነበር። ምኞቴ የሆነ ቦታ ተለውጦ ሌላ ሰው እንዲሆን ነው። ለባለውለታዬ ቁሜ ሁሌም ጥሩ ነው የሚመኝለት።
ቁሜ የሆነ ቦታ ሆነህ ይሄን የምታይ ከሆነ "ባለውለታዬ" በማለቴ እንዳትገረም። አየህ ቁሜ ሁላችንም ልጅነታችን ላይ ነው የምንሰራውም የምንገራውም ብዬ በፅኑ አምናለሁ። አየህ ካንተ በፊት ተበቃይ ማንነት ነበርኝ። ከክፉ ሰው ጋር እየተጋፉም እየተላፉም መኖር አሰልቺ ነገር ነው። ካንተ በኋላ ነው አዲስ ማንነት ያገኘሁት። ክፉን መሸሽ፣ እንዳለ መተውና መርሳትን የተማርኩት ባንተ ነው። እነ እዮቤን የመቅጣት ማንነቴን አንተ አወጣኧው። እሱም መቀጨት ስላለብት አንተው አጠፋኧው። ስለዚህ ሌሎቹን ጓደኞቼን አመስግኑኝ ስል አይተሃል አደል? አንተን ግን እኔ ላመሰግንህ ነው አመጣጤ። ቁሜ ቁምላቸው መቼም ልረሳህ አልችልም ደሞ። የሚኒስትሪ ፎቶዬን ባየሁ ቁጥርና ልብሴን አውልቄ ግራ አጥንቴ መጣመሙን ስመለከት ከቶ ልረሳህ ይቻለኛልን? ሃሃሃ ምኞቴ ስለአንተ መልካሙን ሁሉ መስማት ብቻ ነው። የምሬን ነው ማርያምን። ብቻ እዚህ ቦታ ነኝ አለሁ በለኝ። ያንተው። ለካ ያንተው ስድብ ይምስላል እሺ በቃ የአንተው ተማሪ ነኝ ከዚሁ የሆነ ነገር በለኝ ሃሃሃ
ሉላደይ ዳኛቸው
ስለ ሉላደይ በሰፊው ሌላ ጊዜ አወራለሁ ብያለሁ። አሁን መልህክት ስላለኝ ነው ለሷ። ሉላዲ ሃይ! ከዚ ልጀምርልሽ። እንደምታውቂው የኔ እንግሊዘኛ መፅሃፍ መጥፋቱን መጀመሪያ የነገርኩት ለአንቺ ነበር። አርብ ለት በቦርሳዬ ጎል ሰርተን ኳስ ስንራገጥ የሆነ ሰው ከነ ቦርሳዬ መጽሃፌንም ይዞት ሄደ። ቅዳሜ ቤት ተናግሬ እሁድ ሌላ መጽሃፍ ከአጠና ተራ ተገዝቶልኝ ነበር። የኔ መፅሃፍ መጥፋት ታሪክ እዚህ ጋር ያበቃ መስሎኝ ነበር። ላንቺ ሰኞ መጥቼ ስነግርሽ ጠፋብኝ እንጂ ገዛው ጋር ሳልደርስ "ይጥፋኣ! ጦስህን ይዞህ ይሂድ! የኔን ለሁለት እንጠቀማለን" አልሺኝ። የኔ ንጋት አበባ! የኔ ፈጥኖ ደራሽ! እንዴት እንደኮራሁብሽ ብታይ! አቅፈህ ግጥም አርገህ ሳማት የሚለውን ስሜቴን ተቆጣጥሬው ነው ዝም ያልኩሽ። ስወድሽ እኮ!
ደሞ ቃልሽን ጠባቂ ነበርሽ። በስንተኛው ቀን ላይ "ዛሬ ያንተ ተራ ነው" ብለሽ እንግሊዘኛ መፅሃፍሽን ሰጠሺኝ። እንዳላሳፍርሽ ብዬ ተቀበልኩሽ። ግን ቆይቼ ሳስበው እኔ መፅሃፍ እያለኝ አንቺን መጽሃፍ መንሳት የበለጠ ልክ እንዳልሆነ ሲገባኝ "ረስቼው ነው። ከሰፈር ለሳምንት የተዋስኩት መፅሃፍ አለ። ሳምንት ትሰጪኛለሽ ብዬ መለስኩልሽ። በሶስተኛው ቀን "መጽሃፉን ቦርሳ ውስጥ አጣሁት እዚህ ረስቼው ነበር እንዴ?" ብለሽ ስትይኝ "አረ ቦርሳሽ ውስጥ ከትቼዋለሁ በደንብ ፈልጊው" ስልሽ የተቆፈረልኝን ጉድጓድ ምኑንም አላሰብኩም ነበር።
በዚ መሃል ነው እንግዲህ ሌባ ተብዬ ያንቺን መጽሃፍ ይዤ የተገኘሁት። ሌብነቴ የእውነት ቢመስልሽም አልፈርድብሽም። ከዛ በኋላም አልተለወጥሽብኝም። እኔ እንዳልሰረኳት ማስረጃ ሳይኖረኝ አልነግራትም ብዬ እያሰብኩ ሳለ ነው ሌብነት ጥሩ እንዳልሆነ እጅግ ኮስተር ብለሽ የመከርሺኝ። አመካከርሽን ወድጄው ይምስለኛል እንደ ሌባ ሰማሁሽ። እንደውም በጣም ነው ደስ ያለኝ። ሉላዲ እንካ ብላ የሰጠቺኝን መጽሃፍ የምሰርቅ፣ ከንቱ ሰው ብሆን እንኳ፣ ለኔ ያላት ቦታ የማይቀየር ዕንቁ ሴት ምንስ ብትመክረኝ አልሰማም?። ደግሜ እንዳልሰርቅ ቃል ካስገባሺኝ በኋላ ላንቺ መንገሩን ደግሜ እንዳላስበው አድርጌ፣ እርግፍ አርጌ ተወኩት። ቃልሽን ግን ጠብቄያለሁ። ያኔም ባልሰርቀም ከዛም በኋላ እንኳን መስረቅ ይቅርና አንድም ቀን ለመስረቅ ሁላ አስቤ አላውቅም። ያንቺ ውጤት ነኝና ከልቤ አመሰግንሻለሁ። ይሄን ለመንገር 25 አመት ሙሉ ለምን እንደፈጀብኝ የጊዜ አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው።


